ወንጌል ባመኑት ላይ ብቻ ሳይሆን የሰሙት ሁሉ ላይ ያለው ተጽዕኖ ጥልቅ እንደሆነ ዕሙን ነው፤የወንጌሉ ባለቤትም ክርስቶስ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ የሆነን ለውጥ በማምጣት ታሪክ የሚያወሳው ብቻ ሳይሆን የሚወዳደረው የሌለ ነው፡፡ የክርስቶስ ሙሽራ የሆነችው ቤተ-ክርስቲያን ይህንን ስራ ለመቀጠል በምድር ላይ ኃላፊነት ያለባት ብትሆንም፤አንድ የህንድ ማህራጅ የተናገረው ያለንበት እውነታን ያብራራዋል ‹ክርስቶሳችሁን እወደዋለው፤እናንተ የእርሱን ክርስቲያኖችን ግን አልወዳችሁም› በማለት በአለም ዕይታ ያለውን የክርስቶስን ታላቅ ማንነት እና በክርስቲያኖች መካከል ያለውን ድክመት አመላካች ነው፡፡ ቤተ-ክርስቲያን በአላማዋ አለመኖር፤አለም ክርስቶስ እንዲሸፈንባት ምክንያት በመሆን የእግዚአብሔር መንግስት እንዳይሰፋ ሆኗል፡፡

በምድር ላይ እውነተኛ ለውጥ በሁሉም አቅጣጫ ይታይ ዘንድ ቤተ-ክርስቲያን ክርስቶስን በሚገባ መልኩ መምሰልም ሆነ መወከል ይጠበቅባታል፡፡

ትውልድን የማብቃት አለም አቀፍ ሁለንተናዊ አገልግሎት በተለያዩ የህይወት ምህዳሮች ላይ ተጽዕኖን በማምጣት የለውጥ ምክንያት የሆኑ ሰዎችን ዱካ በመከተል የተቋቋመ ሲሆን፤የመጽሐፍ ቅዱስን መሰረታዊ አስተምሮን ማዕከል በማድረግ የክርስቶስን ወንጌል ለአለም ሁሉ ደርሶ ማየት ዋና አላማችን ነው፡፡ይህም የክርስቶስ ወንጌል አዋጅ ለሰዎች የማዳንን ወንጌል መናገር ፣ደቀ-መዛሙርትን ማፍራት እና የአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያን አገልግሎትን ማጠናከር፣እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን የሚያካትት ስራ እንደሆነ በማመን የክርስቶስን ፈለግ በምድር ላይ እንከተላለን፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን አገልግሎት የእግዚአብሔርን መንግስት ስራ ለማሳካት በምድር ላይ ያለውን የአገልግሎት ህይወት ማቴዎስ በሚከተለው መንገድ ይገልጸዋል ‹ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።› ማቴ 4፡23 ይህንን አገልግሎት በሚከተለው መንገድ ወንጌል መር የሆነ ለውጥ በሰዎች ህይወት ውስጥ እንዲሰርጽ አብራችሁን ትሰሩ ዘንድ እንጋብዛለን፡፡